ሠዎችን ክፉ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው?

4th July 2016  By Melody Sundberg
0


በአቤል ዋበላ ከእንግሊዘኛው የተተረጎመ

የማሰቃየት ተግባር (Torture) ጭቆናን እግር ለእግር ተከትሎ የሚመጣ ልማድ ነው፡፡ ምንም እንኳን ምክንያቶቹ እና መንገዶቹ ቢለያዩም፣ አንድ ነገር ግልጽ ነው፡፡ የማሰቃየት ተግባር በብዛት የሚደረግ ሲሆን ብዙዎችም ለዚህ አሰቃቂ ነገር የተጋለጡ መሆናቸው ነው፡፡

ማሰቃየት ተግባርጥንት እና መካከለኛው ስልጣኔ ጀምሮ እሰከ አሁን ዘመን ድረስ ሲከናወን የነበረ ነው፡፡ ውሎ አድሮ ተዓማኒ ያልሆነ የእምነት ቃል ማወጣጫ መንገድ መሆኑ ሰለተደረሰበት በአውሮጳ መንግስታት እንዳይከወን ታግዷል፡፡ በኋላም ይህ ተግባር በተባበሩት መንገስታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የተወገዘ ሆኗል፡፡ እንደ አምነሲቲ ኢንተርናሽናል መረጃ 156 ሀገራት የተባበሩት መንግስታቱን ፀረ የማሰቃየት ተግባር ድንጋጌ ተስማምተው ፈርመዋል፡፡ ምንም እንኳን እነዚህ እርምጃዎች ቢወሰዱም የማሰቃየት ተግባር አሁንም የተለመደ የማስፈራሪያ፣ የማስገደጃ እና የመቅጫ መንገድ ሆነ እያገለገለ ነው፡፡

ከሰለባዎች በቀጥታ የተገኙ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የሚያወሱ በርካታ ታሪኮች በአንቶልድ ስቶሪስ ለንባብ በቅተዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ እነዚህ ታሪኮች መስማት ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ የማሰቃየት ተግባር የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ አንድ አካል ነበር፡፡ አብዱላሂ አጋላጭ(whistleblower) ሲሆን በኦጋዴን የተፈጸሙ አሰቃቂ የማሰቃየት ተግባሮች፣ መፈጸማቸውን የሚያስረዱ ማስረጃዎችን በመሰብሰብ እንዲታተሙ አድርጓል፡፡ የጆማኔክስ ጓደኞች የሆኑት የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች ስለሰብዓዊ መብቶች በመጦመራቸው ምክንያት ለማሰቃየት ተግባር ተጋልጠዋል፡፡ ገጣሚው ጫላ ስለ ኦሮሞ ህዝብ የሚያወሱ ግጥሞች በመጻፉ ምክንያት እጅግ በጣም የከፋ የማሰቃየት ተግባርን ተቋቁሞ ማለፍ ነበረበት፡፡ ዘላለም፣ ባህሩ እና ዮናታን የዲጂታል ደኅንነት ስልጠና ለመውሰድ በማመልከታቸው ምንም እንኳን ስልጠናው ባይካሄድም በእስር ቤት ሳሉ ለማሰቃየት ተግባር ተጋልጠዋል፡፡ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በታፈነበት በየትኛውም ስፍራ ጨቋኞች ህዝቡን ዝም ለማስባል የማሰቃየት ተግባርን እንደመሳሪያ ይጠቀማሉ፡፡

ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በታፈነበት በየትኛውም ስፍራ ጨቋኞች ህዝቡን ዝም ለማስባል የማሰቃየት ተግባርን እንደመሳሪያ ይጠቀማሉ፡፡

የማሰቃየት ተግባር በተፈጸመበት በየትኛውም ስፍራ የማሰቃየት ተግባሩን የሚፈጽም ሰው ይኖራል፡፡ በአብዛኛዎቹ ጉዳዮች የማሰቃየት ተግባሩን የሚፈጽሙት መርማሪዎች፣ ወታደሮች፣ ዋርድያዎች እና ሌሎች የደህንነት ሰዎች ናቸው፡፡ ይህንን የጭካኔ ተግባር ለምን ይፈጽማሉ? ሲወለዱ ጀምሮ ክፉ ስለነበሩ ነው ወይስ በኋላ ነው ክፉ የሆኑት? ከጥቂት ጊዜ በፊት በማኀበራዊ ሚዲያ ሰዎች ለምን ክፉ ይሆናሉ የሚል ጥያቄ አንስቼ ነበር፡፡ ፍቅረ ነዋይ፣ ፍርሃት፣ የስልጣን ጉጉት፣ ስብግብግብነት እና ደካማነት ካገኘኋቸው መልሶች ውስጥ ከፊሎቹ ናቸው፡፡ ምን አልባት ፍቅረ ነዋይ እና ስግብግብነት የተወሰኑትን ምክንያቶችን ያብራሩ ይሆናል  ተጨማሪ ምክንያቶች መኖራቸውን ግን እርግጠኛ ነኝ፡፡

የምርምሮች ውጤቶች እንደሚገልጹት የማሰቃየት ተግባር ለምን እስካሁን ድረስ እንደሚፈጸም የሚያሳዩ በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ በተደጋጋሚ ከሚጠቀሱ ምክንያቶች አንዱ ሆኖ መቅረቡን የቀጠለው ይህ ነው፤ የተወሰኑ ሰዎች “ጠላቶች” ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ እነዚህ “ጠላቶች” እንደ ወንጀለኞች አድርገው በሚቆጥሯቸው የማሰቃየት ተግባር ፈጻሚዎች ሰብዓዊ ክብራቸው ይገፈፋል፡፡ ተገልሎ መታሰር ስለሚኖር ወይም ገለልተኛ የሆነ የህክምና ምርመራዎች አለመኖር የማሰቃየት ተግባር ለሚፈጽሙት ሰዎች በተግባራቸው መቀጠሉን ቀላል ያደርግላቸዋል፡፡ ሦስተኛው ምክንያት ብርቱ የሆነ አክብሮት ለባለስልጣኖች ሰለሚኖራቸው የማሰቃየት ተግባር ፈጻሚዎቹ ያለምንም ጥያቄ ለእነርሱ ይታዘዛሉ፡፡ ነገር ግን ዋናው ምክንያት የማሰቃየት ተግባሩን የሚፈጽሙት ሰዎቹ እራሳቸው ናቸው፤ የማሰቃየት ተግባር ፈጻሚው እና የእርሱ/የእርሷ ስልጣን፡፡

የማሰቃየት ተግባር እንዲቆም ከፈለግን ለምን እንደሚፈጸም በትክክል መረዳት አለብን ብዬ አምናለው፡፡ ሌሎች ሰዎች ይህን ተግባር መቼም ፈጽመው ሳያውቁ አንዳንድ ሰዎች ለምን ይህን የማሰቃየት ተግባር ፈጻሚ እንደሚሆኑ ልንረዳ ይገባል፡፡ ምን አልባት የዚህ መልስ በሰው ልጅ ስነ ልቦና ውስጥ ይገኛል፡፡

አንቶሎድ ስቶሪስ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በማሰቃየት ተግባር ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ በጸደይ አንዳንድ ሰዎች ለምን የማሰቃየት ተግባር እንደሚፈጽሙ ከስነ ልቦና ሳይንስ አንጻር የሚያብራሩ ተከታታይነት ያላቸው ጽሑፎችን እናትማለን፡፡ ጽሑፎቹ ባለስልጣናት እና ሀይል በእጃቸው ያለ ቡድኖች እንዴት ሰዎች የሞራል ስሜታቸውን እንዲያጡ እንደሚያደርጉ፣ የማሰቃየት ተግባር ፈጻሚዎች እንዴት እንደሚሰለጥኑ እና ሰለባዎቹ እንዴት ሰብዓዊ ክብራቸው እንደሚዋረድ ይነግሩናል፡፡ በቀላሉ ለማስቀመጥ፣ የክፉ ሰዎችን ስነ ልቦና የመረዳት ጊዜው አሁን ነው፡፡

 
Melody Sundberg
Project manager of Untold Stories. Photographer and artist. Educated in Psychology.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *


More Story
የፌስቡክ ገጼ በደም ጨቀየ በአቤል ዋበላ ከእንግሊዘኛው የተተረጎመ ማለቂያ የሌላቸው የቆሰሉ እና የሞቱ...