ሦስት ሃገራት-ሦስት ምስስሎሽ

9th January 2017  By Melody Sundberg
0


በአንድ ወቅት የፀረ ሽብር ህጎች ጋዜጠኞችን ለማሰር ይውሉ ይሆናል የሚል ስጋት በሰዎች ዘንድ ነበር። ዛሬ ይህ አስፈሪ ህልም እውን እንደሆነ አይተናል፤ ዛሬ የሽብርተኞች ፍራቻ ወደ ነፃ ሪፖርት/ዘገባ ስራ ፍራቻ ዞሯል። ግብፅ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ በአንድ አህጉር ከመገኘት ያለፈ ምስስሎሽ አላቸው:- የሽብርተኝነት ፍራቻ ወይም ይህን ተገን ያደረገ ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም እነዚህን ሃገራት የአፍሪካ ቀንደኛ ጋዜጠኛ አሳሪ ሃገራት አድርጔቸዋል።

አንድ ፎቶግራፈር ፎቶ በማንሳቱ ታሰረ ቢባል የማይረባ ቀልድ ይመስላል። አለመታደል ሆኖ አስፈሪው እውነታ ይሄ ነው። በግብፅ ሻውካን የሞት ቅጣት እየጠበቀው ነው። ይህ ወጣት የፎቶ ጋዜጠኛ የፀጥታ ሃይሎች የሃይል ምላሽ የሰጡበትን በካይሮ የተካሄደ ተቃውሞን ለመዘገብ በቦታው በመገኘቱ ነው ተይዞ ለእስር የተዳረገው። ይህ እስር ሻውካንን አስደንጋጭ ከሆነው 23 የታሰሩ ጋዜጠኞች ብዛት መካከል አንዱ ያደርገዋል። ታስሮ የሚገኘው በአስፈሪነቱ በሚታወቀው ቶራ እስር ቤት ሲሆን በዚህ እስር ቤት በህክምና አገልግሎት ግድየለሽነት ምክንያት ታሳሪ መሞቱ ተዘግቧል።

ሽብርተኝነትን መዋጋት አስፈላጊ ነው ሆኖም ‘ሽብርተኝነት’ ማለት ምን ማለት ነው የሚለው ላይ የተለያዩ እሳቤዎች አሉ። በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ የሚገኘው አገዛዝ ጋዜጠኞችን እና የተቃውሞ ድምፆችን ለማፈን እና ለማሰር የፀረ ሽብርተኝነት ህጉን ይጠቀማል ወይም ያለአግባብ ጥቅም ላይ ያውለዋል። ይህን በማድረግም አገዛዙ ሚዲያውን የህዝብ ድምፅ ሳይሆን የገዢዎች ድምፅ ብቻ እንዲሆን እንደሚፈልግ በግልፅ አሳይቷል።

በአለፈው አንድ አመት ውስጥ ብቻ መንግስትን በመቃወማቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፤ ታስረዋል። የታሰሩት በአብዛኛው ወደ ሚሰቃዩበት እና ያልፈፀሙትን ነገር እንዲያምኑ ወደሚገደዱበት ማእከላዊ ምርመራ ማእከል ይዘዋወራሉ። ብዙውን ጊዜም መጨረሻቸው ቃሊቲ፣ ቂሊንጦ ወይም ዝዋይ እስር ቤት ይሆናል። እዛም ለበርካታ አመታት ሊቆዩ ይችላሉ። በአብዛኛውም ያለምንም ፍርድ። ከነዚህ መካከል አንዱ በ2003 የታሰረው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ነው። የ18 አመታት እስራት ተፈርዶበታል።

ኤርትራውያን በስዊዲን ጥገኝነት ጠያቂዎች ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር ከሚይዙት መካከል ናቸው። ስዊዲናውያን በኤርትራ ከታሰረ 15 አመታት ስላስቆጠረው ስለ ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ ሰምተው ሊያውቁ ይችላሉ። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጋዜጠኛ ዳዊትን ብቸኛው ስዊዲናዊ የህሊና እስረኛ እንደሆነ እውቅና ሰጥቶታል። ሆኖም ግን የፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ የጋዜጠኞች አደን በዳዊት ብቻ የተወሰነ አይደለም። የኤርትራ መንግስት በአለም ላይ ከፍተኛ ሳንሱር አድራጊ ከሆኑ 10 ሃገራት መካከል አንዱ ነው። የመንግስት ሚዲያ ብቻ የተፈቀደባት ቢሆንም በዚህ የመንግስት ሚዲያ ውስጥ የሚሰሩ ጋዜጠኞች ህይወታቸውን የሚገፉት በእስር ስጋት ውስጥ ሆነው ነው። ኤርትራ በአለማችን ላይ ከሚገኙ በጣም ጨቌኝ ሃገራት መካከል አንዷ ናት።  ኢንተርኔት በመንግስት ቁጥጥር ስር ሲሆን መንግስት የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ላይ ክትትል እንደሚያደርግ ይታመናል። በግል ጭውውቶች መካከል እንኴን የመንግስት ወሬ አቀባዮች እንዳይሰሙ ካለ ፍራቻ የተነሳ ሰዎች ጥንቃቀቄ ያደርጋሉ። ጭቆናው ሃሳብን በነፃነት መግለፅ ላይ ብቻ አያበቃም። ከተፈቀዱት አራት ሃይማኖቶች (ኦርቶዶክስ ክርስትያን፣ የሮማ ካቶሊክ፣ ኢስልምና እና ሉተራን) ውጪ ሌላ ሃይማኖት የሚከተሉ ሰዎች ለከፍተኛ መሳደድ ስቃይ/ግርፋት እና እስር ይጋለጣሉ። ሌላው ሰዎችን ሃገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ የሚዳርጋቸው የግዳጅ የውትድርና አገልግሎት ነው። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በአስቸጋሪ አያያዙ ወደሚታወቀው ሳዋ የውትድርና ስልጠና ማእከል ይላካሉ።

ብዙ ሃገራት ጥቂቶች ብቻ ተናግረው አብዛኞች ወደሚታፈኑበት እውነታ እየተጔዙ ነው፤ የትርክቱ አንዱ ጎን ብቻ ተነግሮ ሌላው ሳይነገር የሚቀርበት። ይህ በጣም አስፈሪ ሂደት ነው። ክፍት አሰራርን ዲሞክራሲን እና ግልፅነትን አልሞ ከመስራት በተፃራሪው አንዳንድ መንግስታት ወደ ሳንሱር ሚስጥራዊነት እና ሙስና ከፍተኛ እርምጃዎችን ያደርጋሉ። የምእራቡ አለምም ስለነዚህ ሃገራት በጣም ያውቃል እንዲሁም ያሉበት ሁኔታ ‘ያሳስበዋል’። በተግባር ግን የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎችን መብት ለማስከበር በሚያስችል ደረጃ አላሳሰባቸውም። ስትራቴጂያዊ ግንኙነቶችን ማጠናከር ከሰብአዊ መብቶች የበለጠ ዋጋ ያለው ይመስላል።

ይህን ሁኔታ የመለወጥ ጥያቄ ለመንግስት ብቻ የሚተው አይደለም። የምንኖርበት አለም በዙሪያችን የሚደረጉ ነገሮችን የማናውቅበት፣ ሙስና ሳይጋለጥ የሚቀርበት፣ ተቃራኒ ሃሳቦች የማይደመጡበት እና ዜጎች መሪዎቻቸውን የማይተቹበት እንዲሆን እንፈልግ እንደሆን ሁላችንም እራሳችንን መጠየቅ አለብን። ሰዎች ድምፃቸው በማይሰማበት አለም ውስጥ መኖር እንፈልጋለን? ከነዚህ ዝግ በሮች ጀርባ ምን እየተካሄደ እንደሆነ ለማሰብም አልደፍርም። ምናልባትም ግብፅ ከኢትዮጵያው የፀረ ሽብርተኝነት ህግ ተነሳሽነትን ወስዳለች። ከግብፅ ተነሳሽነትን የሚወስደው ቀጣዩ ሃገር ማን ይሆን?

የተግባር ጊዜው አሁን ነው። ይሄን ሂደት ለማስቆም ሁሉም ሰው አንድ ነገር ማድረግ ይችላል። የሰብአዊ መብት ጥሰት በራሳቸው ላይ የደረሰባቸውን ሰዎች ከራሳቸው በመስማት እንጀምር፣ ለራሳችንም እንድንጠነቀቅ። ኤርትሪያ የጭቁኖች ሃገር የሚለውን የኤዶዋርዶ ኢያኮቤሊ ፅሁፍ እንዲሁም የሲሉናስን ኢፍትሃዊ ሦስት አመታት-የመሃመድ አቡ ዘይድ ‹‹ሻውካን››ን ነፃነት እንፈልጋለን የሚሉ ፅሁፎች ያንብቡ፡፡ እነዚህን ታሪኮች ለሌሎች እናጋራ።እናከናውንም ብዙሃኑ እውነታውን መረዳት ሲችሉ መጥፎውን ሂደት ከመስፋፋት መግታት ስለሚቻል።

የድርሻችንን እንወጣ።
Melody Sundberg
Project manager of Untold Stories. Photographer and artist. Educated in Psychology.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *


More Story
Untold Stories on Oromo Media Network OMN Untold Stories project manager Melody Sundberg was hosted on OMN on December 18, 2016. Support Untold Stories Crowdfunding...