ዳዊት ሰለሞን፣ ስደተኛው ጋዜጠኛ፤ ‹‹ስሜን ጨምሮ ሁሉንም ነገር እያጣሁ እንደሆነ እየተሰማኝ ነው››

26th November 2015  By Fasil Girma
0


This article is available in English here.

ጸሐፊ፤ ፋሲል ግርማ
ተርጓሚ፤ በፍቃዱ ኃይሉ

የ24 ዓመቱ ሰዋለም ታዬ በጎረቤት አገር ኬንያ በስደት ላይ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ነው፡፡ አገሩን ጥሎ ከወጣ እና አዲሱን ሕይወቱን ከጀመረ ዘጠኝ ወር ሞላው፡፡ በኢትዮጵያ፣ ሙያው የሆነውን የሚዲያ ሥራ ጥሎ ለመሰደድ ተገዷል፡፡ ለአምስት ዓመታት ከዘለቀ ባለብዙ ደርዝ ተግዳሮቶች በኋላ ተፅዕኖውን ተቋቁሞ መቀጠል አልቻለም፡፡

‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ከሁሉም ተፅዕኖ ፈጣሪ የግል ፕሬስ ኋላ ሁኖ በብልሀት ያፍናቸዋል፡፡ ነጻ የመረጃ ፍሰት ብሎ ነገር በሀገሪቱ የለም›› ይላል ሰዋለም፡፡

ሰዋለም የጋዜጠኝነት ሥራውን የጀመረው በዝነኛዋ ጋዜጣ ‹‹ፍትሕ›› ላይ ነበር፡፡ በሰኔ 2004፣ ፍትሕ ጋዜጣ መንግሥት ከማሳወቁ አንድ ወር ቀደም ብላ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሞት የሚመለከት ጽሑፍ አተመች፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ገዢ ፓርቲ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግምባር (ኢሕአዴግ) 35,000 የፍትሕ ጋዜጣን ቅጂ ከመሰራጨቱ በፊት በእሳት አጋዩት፡፡ ይህ የጋዜጣዋ መጨረሻ ሆነ፡፡ ጥቅምት 2007፣ ማለትም ፍትሕ ጋዜጣ ከታገደች ከ3 ዓመት በኋላ የጋዜጣዋ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ ስም በማጥፋት ክስ 3 ዓመት ተፈርዶበት ወኅኒ ወረደ፡፡ አሁንም እስር ላይ ይገኛል፡፡

‹‹በመጣጥፎቼ ምክንያት ተመትቼያለሁ፣ የተለያዩ ጊዜያት ታስሬያለሁ፣ ማስጠንቀቂያ ደርሶኛል፣ ብሎም ሥራዬን ለማቆም ተገድጃለሁ›› ይላል ሰዋለም፡፡

ፍትሕ መታገድ በኋላ፣ ሰዋለም እና ባልደረቦቹ ሌሎች 3 ጋዜጦችን ማሳተም ጀመሩ፡፡ ኢሕአዴግ አንዱን ሲዘጋባቸው፣ ሌላኛውን ይከፍታሉ፡፡ ነገር ግን፣ ይህ ቀላል ሥራ አልነበረም፡፡ ሰዋለም እና ሠራተኞቹ በዚህ ጊዜ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡

‹‹በመንግሥት የደኅንነት ኃይሎች ክትትል ውስጥ ማለፍ የዕለት ተዕለት ኑሯችን ነበር፡፡ በሁሉም ነገር ግልጽ ነበር፡፡ ሥራችንን እንድናቆም የሚያስጠነቅቁ የሥልክ ጥሪዎች እና የጽሑፍ መልዕክቶች የተለመዱ ነበሩ፡፡ በማይታወቁ ሰዎች፣ ነገር ግን የደኅንነት ሰዎች መሆናቸው ግልጽ በሆኑ ሰዎች እንደበደባለን፡፡ አንዳንዴ፣ እኔና ጓደኞቼ በአስቀያሚው እስር ቤት ማዕከላዊ ሁለት ወይም ሦስት ቀናት ገብተን እንወጣ ነበር፡፡ በፖለቲካዊ ግፊት የተለያዩ ክሶች በየጊዜው ይከፈትብን ነበር፣›› ይላል ሰዋለም፡፡

የ38 ዓመቱ ዳዊት ሰለሞንም የስደትን ኑሮ ከሚስቱና ከሁለት ልጆቹ ጋር በናይሮቢ፣ ኬንያ እየገፋ ነው፡፡ በሚዲያ ሥራ ከ10 ዓመት በላይ አገልግሏል፤ እሱም እንደሰዋለም፣ ወደሃገር ቤት ለመመለስ እከሰስ ወይም እታሰር ይሆን የሚል ስጋት አለበት፡፡ ዳዊት፣ በፕሬሱ የመሥራትን ፈተና ሲገልጸው እንዲህ ይላል፣

‹‹በኢትዮጵያ የሚዲያ ሥራ የባለሙያነት ችግር አለ፡፡ መንግሥት ነጻ ፕሬሱን እና ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን ለማሸማቀቅ ያለመ እንግዳ የሆነ የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ አውጥቷል፡፡ የተለያዩ የግል ዓላማ ያላቸው ትናንሽ ቡድኖች ፕሬሱን አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድረውበታል፡፡ ሀብታሞች፣ መንግሥት እና ፖሊስ በሚዲያ ሥራ ውስጥ ለግል ፍላጎታቸው ሲሉ በቀጥታ ጣልቃ ገብተውበታል፡፡››

 

የፕሬስ ነጻነት እጦት በኢትዮጵያ

ከሰዋለም እና ዳዊት ውጪ፣ ሌሎች ከ30 በላይ የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች በኬንያ ይገኛሉ፡፡ ብዙዎቹ ወደኬንያ የመጡት በ2006 መጨረሻ ላይ ነው፡፡ ይህ ወቅት የኢትዮጵያ ምርጫ የተቃረበበት እና የኢትዮጵያ መንግሥት በግል ፕሬሱ ላይ ጫናውን ያበረታበት ጊዜ ነበር፡፡ ዓላማቸው የትችት ድምፆችን በማፈን ገዢው ፓርቲ ለአምስተኛ ጊዜ ምርጫውን እንዲያሸንፍ ማድረግ ነው፡፡

መቀመጫውን ኒውዮርክ ያደረገው የጋዜጠኞች ተቆርቋሪ ኮሚቴ (ሲፒጄ) በቅርቡ በለቀቀው ሪፖርቱ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሳንሱር ከሚደረግባቸው የዓለም አራት አገራት አንዷ ናት፡፡ ሪፖርቱ እንደሚለው ‹‹ኢትዮጵያ ለ2007 ምርጫ ዝግጅት ጋዜጠኞችን፣ ማተሚያ ቤቶችን እና አከፋፋዮችን በማሰርና በማዋከብ ቀሪ የአገሪቱን ነጻ የሕትመት ውጤቶች በዘዴ አዳክማለች፡፡››

ሪፖርተርስ ዊዝአዊት ቦርደርስ በተባለ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ማኅበር የሚያዘጋጀው የዓለም የፕሬስ ሰንጠረዥ ላይ ኢትዮጵያ ከ180 አገራት መካከል 142ኛ ሆናለች፡፡ ሰንጠረዡ፣ አገራትን በፕሬስ ነጻነታቸው፣ በዜና አውታሮቻቸው ነጻነት፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪዎች እና ሌሎችም ጉዳዮች አገራትን በደረጃ በየዓመቱ ያስቀምጣል፡፡ ከሰንጠረዡ ወደሥር ያሉ አገሮች በፕሬስ ነጻነት ጉዳይ ጥሩ ያልሠሩት ናቸው፡፡ ሪፖርቱ እንደሚለው ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት የሚዲያ ጭቆናውን በ2006 የተወሰነ ደረጃ ከፍ አድርጎታል፡፡ የቃል እና የአካል ጥቃቶች፣ የወንጀል ክሶች እና ግምድል ፍርዶች፣ ከ2007ቱ ምርጫ ቀደም ብሎ ባለው ጊዜ ታይቷል፡፡ የተሳካላቸው ይመስላል፡፡ ከ6 በላይ ጋዜጦች የተዘጉ ሲሆን፣ ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ ከ30 በላይ ጋዜጠኞች አገር ለቀው መሰደዳቸውን መዝግቧል፡፡ እንዲያም ሆኖ፣ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ እርዳታ በማግኘት ከአፍሪካ አገራት ቀዳሚዎች ውስጥ ናት፡፡››

ምርጫው ግንቦት 15፣ 2007 ተጠናቋል፡፡ እንደኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቂያ፣ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ እና አጋር የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሁሉንም የፓርላማ 547 መቀመጫዎች 100 በመቶ – አንድም የተቃዋሚ ፓርቲ አባል አንድም መቀመጫ ሳያገኝ – አሸንፏል፡፡ ገዢው ፓርቲ ‹‹አዲስ›› መንግሥት በመመሥረት የቀድሞውን ባለሥልጣናት ያቀፈ ካቢኔ ሰይሟል፡፡

 

በኬንያ ያሉት ጋዜጠኞች ተግዳሮቶችን መጋፈጣቸውን ቀጥለዋል

ከሶርያ ብቻ በመከተል፣ ኢትዮጵያ በዓለማችን ብዙ ጋዜጠኞች ተሰደው ኑሯቸውን በኬንያ እና በምዕራብ አገራት ያደረጉባት አገር ሆናለች፡፡ ኢፍትሐዊ እስር እና ክስ ሸሽተው ከወጡ በኋላም፣ በኬንያ የሚኖሩት ጋዜጠኞች ሌሎች ፈተናዎች ተጋርጠውባቸዋል፡፡

ብዙዎቹ ስደተኛ ጋዜጠኞች ከኬንያ ፖሊሶች እና በኬንያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል በብዛት በሚገኙት የኢትዮጵያ የደኅንነት ሠራተኞች አሳሳቢ የደኅንነት ስጋት እየገጠማቸው ነው፡፡ የኬንያ ፖሊሶች ስደተኞቹ ጋዜጠኞች በናይሮቢ ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ተገቢ ሰነድ ባለመያዛቸው ያስቸግራቸዋል፡፡ የጋዜጠኞቹ ሕይወትና ነጻነት፣ ቀንም ሆነ ማታ ከቤት መውጣት ባለመቻላቸው ክፉኛ ተገድቧል፡፡

የ28 ዓመቱ ስደተኛ ጋዜጠኛ ተስፋዬ ጎሳዬ (ሥሙ ለደኅንነቱ ሲባል ተቀይሯል)፣ ኬንያ ውስጥ ስደተኛ ሆኖ የመኖርን ፈታኝነት ይዘረዝራል፣

‹‹ወደዚህ የመጣሁት ከሚስቴና ከሦስት ዓመት ሴት ልጄ ጋር ነው፡፡ የቋንቋ ችግር አለብኝ፣ በዚያ ላይ የመጣሁት እኔ ከማውቀው ሙሉ ለሙሉ የተለየ ባሕል ወዳለው ማኅበረሰብ ነው፡፡ ልጄ የምትናገረው አማርኛ ብቻ በመሆኑ እዚህ ካሉት ሕፃናት ጋር አብራ መጫወት አልቻለችም፡፡ ማንም እዚህ የእኛን ቋንቋ አይናገርም፡፡ አዲስ አበባ ያሉትን ጓደኞቿን ስለምትናፍቅ መልሰን እንድንወስዳት እኔና እናቷን ደጋግማ ትጠይቀናለች፡፡ ትምህርት ቤት እንዳላስገባት አቅም የለኝም፡፡ ከተማው ውስጥ መንቀሳቀስ የማይታሰብ ነው፡፡››

የሆነ ጊዜ፣ ተስፋዬ የሚስቱን እና የራሱን የጋብቻ ቀለበት በመሸጥ የቤት ኪራይ ለመክፈል እና የቤተሰቡን ወጪ ለመሸፈን ተገድዷል፡፡

ሁሉም የኬንያ ስደተኞች ማለት በሚቻልበት ሁኔታ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተና ኮሚሽን (ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር.ን) ሒደትን ከሦስተኛው ዓለም ወደ አሜሪካ ወይም የአውሮፓ አገራት ለመሄድ መጠበቅ አለባቸው፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም ሁኔታ እና ግለሰብ በዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር. የሚታየው ተራ በተራ እና ለምን ያህል ጊዜ በሚፈጅ ሒደት እንደሆነ በማይታወቅ አካሄድ ነው፡፡

ከፈታኙ እና የማያልቀው ሕጋዊ ትግል ባሻገር፣ የዳዊትን የስደት ሕይወት የሚገዳደረው ጥሎት የሄደው ነገር ሁሉ ቁጭት ነው፡፡

‹‹አገሬን እናፍቃለሁ፡፡ መሬቱን አይደለም፤ አገሬ ያላትን ሁሉ ነው የምናፍቀው፡፡ ከባሕር የወጣ አሳ የሆንኩ ያክል ነው የሚሰማኝ፡፡ ስሜን ጨምሮ ሁሉን ነገር ያጣሁ ያህል ይሰማኛል፡፡ እዚህ ለዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር. ሳመለክት፣ ጉዳይ መከታተያ ቁጥር ሰጡኝ፤ ቁጥር ብቻ፡፡ አገር ቤት ሳለሁ ሥም ነበረኝ፡፡ ሕልሜ ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር፤ ዜጋ ነበርኩ፡፡ አሁን ሁሉንም ነገር እያጣሁት ነው፡፡

‹‹ጓደኞቼ አሉ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለፕሬሱ ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ጋዜጠኞች ባልደረቦቼ አሉ፡፡ ብዙዎቹ ጋዜጠኞች ታስረዋል፡፡ ለሕይወቴ ፈርቼ ጥያቸው ከአገር በመውጣቴ ሐፍረት እና ፀፀት ይሰማኛል፡፡››

ሰዋለምም እንደዳዊት ነው የሚሰማው፡፡

‹‹የመሰደድ ዕቅዱ አልነበረኝም፤ የመጨረሻ ደቂቃ ውሳኔ ነው፡፡ መጀመሪያ ያስጨነቀኝ ፊቴ የተደቀነውን እስር እንደምንም ብሎ ማምለጥ መቻል ብቻ ነበር፡፡ ከዚያ ሙያዬን እና አሁንም እዚያው ያሉ ጓደኞቼንና ከመታሰር አስፈሪ ስጋት ጋር የተፋጠጡ ሌሎችንም የመክዳት ስሜት ተሰማኝ፡፡››

በነዚህ ሁሉ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እያለፉም ቢሆን ጋዜጠኞቹ የተለየ ችግር የገጠመውን ሰው በጋራ ሆነው በማገዝ እየኖሩ ነው፡፡ አንዳቸው ማግባት የፈለጉ እንደሁ ወይም የቤት ኪራይ መክፈል የቸገራቸው እንደሁ ገንዘብ ያዋጣሉ፡፡ የስደተኞቹን ሕይወት ለማስተካከል ያዋጣሉ፡፡ የሚያስፈልጓቸውን ሰዎች ወይም ድርጅቶች በማገናኘት በኩልም ይደጋገፋሉ፡፡

ስደተኞቹ ጋዜጠኞች በኬኒያ አዲስ ተግዳሮት ገጥሟቸዋል፤ ግን ደግሞ በኢትዮጵያ ፕሬሱን እና ሐሳብን በነጻነት በመግለጽ ጉዳይ ላይ የከፋ ሁኔታ አለ፡፡

‹‹አንድ ሰው ከምንም ተነስቶ የተሻለ ነገር ይመጣል ብሎ ተስፋ አያደርግም፡፡ አዎንታዊ ለውጥ እንዲመጣ የተስፋ መሠረት ያስፈልጋል፡፡ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን በተመለከተ በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የለውጥ ተስፋ አላየሁም፡፡ ሆኖም፣ በተአምር አምናለሁ፡፡ እናም በውስጣዊም ይሁን ውጪያዊ ኃይል የሆነ ለውጥ መምጣት አለበት›› ይላል ዳዊት፡፡

 

 
Fasil Girma
Fasil Girma is an Ethiopian media professional and press freedom advocate. Fasil has more than six years of work experience on both public and private media in Ethiopia. He is currently living in exile in Nairobi, Kenya while freelancing for different media outlets, and advocating for press freedom and the release of imprisoned journalists in Ethiopia.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *


More Story
Torture Reported During Court Hearing of Ethiopian Activists Blogger Zelalem Workagegnehu, along with Yonatan Wolde and Bahiru Degu, have spent 503 days behind bars. Today, they were...