የፌስቡክ ገጼ በደም ጨቀየ

4th July 2016  By Melody Sundberg
0


በአቤል ዋበላ ከእንግሊዘኛው የተተረጎመ

ማለቂያ የሌላቸው የቆሰሉ እና የሞቱ ሰዎችን የያዙ ምስሎች ጎርፍ፣ አልጋ ላይ ወይም መንገድ ላይ የወደቁ ወንዶች እና ሴቶች ምስሎች፣ የተወሰኑት በሚያለቅሱ ሰዎች ሲከበቡ ቀሪዎቹ ደግሞ ብቻቸውን ናቸው፡፡ ከእነርሱ ውስጥ የተወሰኑት በህመማቸው ምክንያት ያለቅሳሉ ይጮኻሉ ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ በተስፋ መቁረጥ አይናቸው ፈጧል፡፡ ያለፉት ጥቂት ሳምንታት የፌስቡክ ዜና መጋቢዬ (my Newsfeed) በደም ጨቅይቶ ነበር፡

የቆሰሉት እና የሞቱት ተቃውሞ አድራጊዎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መዲና የሆነችውን አዲስ አበባን ሀላፊነት በጎደለው መልኩ በማስፋፋት  ለከተማዋ ቅርብ የሆኑ ኦሮሞ ገበሬዎችን ለማፈናቀል መታቀዱን ተችተዋል ፡፡ አብዛኛዎቹ ተቃውሞ አድራጊዎች ከዩንቨርሲቲዎች የመጡ ተማሪዎች ናቸው፡፡ የሚሰማቸው የሆነ ሰው ነበር የፈለጉት፤ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበር ነበር የጠየቁት፤ አሁን ግን ሞተዋል፡፡ ከቅርብ የተነሱ ፎቶዎቻቸው የያዙት አስፈሪ ቁስሎች ሆዴን ህመም እንዲሰማኝ አደረጉ፡፡

በብዙ ሀገሮች እነዚህ ሰዎች ሰላማዊ ሰልፋቸውን ያለ ምንም ማደናቀፍ እንዲያካሂዱ በተፈቀደላቸው ነበር፡፡ የመቃወም መብታቸውም በተከበረ ነበር፡፡ ነገር ግን በሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ አገዛዝ ስር ባለችው ኢትዮጵያ ማንም የተቃወመ፣ የተቸ ወይም መብቱን የጠየቀ ሰው ይታሰራል፣ የማሰቃየት ተግባር ይፈጸምበታል አልያም ይገደላል፡፡ ፌስቡክን ያጥለቀለቁት ምስሎች ግልጽ ቋንቋን ይናገራሉ፡፡ ፖሊስ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የጭካኔ ኃይልን ይጠቀማል፣ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የጥቃት ዒላማ የሆኑት ሰልፈኞች ብቻ አይደሉም ነጻውን ፕሬስ ማፈራረሱም ተጠናክሯል፡፡ ጋዜጠኞች ታስረዋል፣ ባለፈው ሀምሌ እና ጥቅምት በተከታታይ ከእስር የተፈቱት የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎችም ዳግም ወደ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መጥሪያ ደርሷቸዋል፡፡ የ2015 መጨረሻ እና የ2016 መጀመሪያ መልካም አይመስልም፡፡

ነገር ግን አሁንም ተስፋ አለ፣ መንበርከክን እምቢ ባሉ ሰዎች ይቀጣጠላል፡፡ ከቆሰሉ እና ከሞቱ ሰዎች ምስል በተጨማሪ ሌሎች ምስሎችም መታየት ጀመሩ፡፡  የመጡት ከኢትዮጵያ፣ ከአሜሪካ፣ ከስዊዲን፣ ከአውስትራሊያ፣ ከኔዘርላንድ እና ከሌሎች በርካታ ሀገሮች ነው፡፡ ጥቁር ለብሰው እና ፊታቸውን ወደ ምድር ደፍተው ተቃውሟቸውን በዝምታ ማሰማታቸውን ቀጠሉ፡፡ እጆቻቸውን እንደታሰረ ሰው አመሳቅለው፣ ህይወታቸውን እና ነፃነታቸውን ለተገፈፈው ሰልፈኞች አጋርነታቸው አሳዩ፡፡ በአንድ ሀገር ሐሳቡን ለመግለጽ ያልተፈቀደለት ሰው ካለ ማንም ነጻ አይደለም፡፡ ቁርጠኝነኝነታቸው እና መልዕክታቸው ግልጽ ነው፡፡ ክፉው እንዲያሸንፍ አይፈቅዱም፡፡

 

 
Melody Sundberg
Project manager of Untold Stories. Photographer and artist. Educated in Psychology.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *


More Story
Poet Caalaa Hayiluu Abaataa about the Oromo people and the oppression by the Ethiopian government "But the government - of course, it is not a government, actually - is a group of gangsters and mafias, because if someone...